ከስብስቡ ሊቀመንበር የተላከ መልእክት
የሰላም፤ የአንድነት፣ የፍቅር ጥረቱ አሁንም እንደቀጠለ ነው። የምንመኘውን የምንፈልገውን ዘላቂውን ሰላም፤ አንድነት፣ ፍቅር በቤተክርስቲያናችን ብሎም በሕብረተሰባችን ልናመጣ የምንችለው የተለየዩ የመፍትሄ ሃሳቦችን የያዙትን፡ በዳይ ነው የተባለውንም ሆነ ተበድሏል የተባለውን አቀራርበን ውይይት ማድረግ ሲቻልና ብዙሃኑ የተቀበለውን ማስፈጸም ስንችል ብቻ ነው። በሌላ አነጋገር ለችግራችን ዘላቂ መፍትሔ ለማግኘት ሁላችንም የሚያስማማንን መንገድ የመፈለግ ግዴታ አለብን። ይህ ደግሞ ብስለትን፤ ቅንነትን፤ ሐቀኝነትን፣ መተማመንን ይጠይቃል። ፈረንጆቹ እንደሚሉት(MY WAY OR THE HIGH WAY ) ወይም እኔ ያልኩት ካልሆነ እሞታለሁ የሚል አመለካከት ካለ ግን የተነሳንበትን የመወያየቱን መርህ ይገድለዋል።
ይህንን ካልን ዘንዳ!!በዚህም በቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የተነሳው አለመግባባት ደረጃው ይለይ እንጂ ከቤተክርስቲያኑ አስተዳደር ዙሪያ "በደል ደረሰብን፣ መብታችን ተነካ፣ መተዳደሪያ ደንቡ ተሸረሸረ፣ የብዙሃን ድምፅ ታፈነ፣ ሃሳባችን አልተስተናገደም ወዘት በማለት የሚያስቡ ግለሰቦች ለችግራቸው መፍትሄ ነው ያሉትን አቅርበው መወያየት ችለዋል። በውይይቱም ተማምነው የጋራ ኮሚቴ ለማቋቋም በቅተለዋል። አስተማማኝ ሁኔታም እስኪፈጸም ድረስ የተነሱበትን ዓላም እንደማይስቱ አሁንም ለሰላም፣ ለአንድነት፣ ለፍቅር እንደሚታገሉ፣ ሁላችንም ይህንን መርህ ከተከተልን ደግሞ ወደ ነበርንበት መመለሱ ሕልም እንደማይሆን ያምናሉ።
የአንድ አካባቢ ስብስብ ወይንም በብዙሃን ድምፅ የሚተዳደር አካል ለተለያዩ ሃሳቦች መፍትሄ የሚያገኘው ብዙሃኑ ተስማምቶ በተቀበለው ሃሳብ ሲመራ መሆኑን አንጠራጠርም። ይህንን አማራጭ የሌለውን አካሄድ መከተል ደግሞ ግዴታ ነው እንላለን። እስከዛሬ በግልም ሆነ በቡድን በጽሑፍም ሆነ በቃል የተነገሩ ሃሳቦች ሁሉ በእንዲህ ያለ አጠቃላይ ሁሉን አቀፍ ተደጋጋሚ ስብሰባ መቋጨት አለባቸው ብለን እናምናለን።
የዚህ ጦማር አጀማመር ደግሞ ያለምንም መደባበቅ በእውነት ላይ ያተኮረ በቤተክርስቲያን ዙሪያ ያሉትን ችግሮች ሌሎች እንዲረዱት ሃሳቦችን ማንሸራሸር እንዲቻል ከሚያገኘው ጭብጥ በመነሳት አንባቢው ፍርድ መስጠት እንዲችል ለመርዳት ጭምር ነው።
የጦማሩ ባለቤቶች በ 200አባላት የተመረጠው የሰላም አፈላላጊ ኮሚቴ ሲሆን፣ ኮሚቴው እስካሁን ያከናወነውን እያደነቅሁ በዚህም መስክ ጥሩ ተግባር እንደሚያሳይ ጥርጥር የለኝም። አባላቱም የተቻላቸውን ሁሉ በማድረግ ጦማሩ የእውነት መመንጫ የመፍትሄ መፈለጊያ የእውነተኛ ዜና መቀያየሪያ መድረክ እንዲያደርገው ማሳሰቢያዬን በኮሚቴው ስም ላቀርብ እወዳለሁ። በቤተክርስቲያኑ አስተዳደር ዙሪያ የተሰበሰቡት ኃይሎችም ለሰላም፣ ለአንድነት፣ ለፍቅር ጥረቱ በጎ ምላሽ እንዲሰጡ በኮሚቴውና በራሴ ስም ጥሪ አቀርባለሁ።
ቸሩ እግዚአብሔር የሰላም፣ የአንድነት፣ የፍቅር አቅጣጫ ያሳየን።
የስብስቡ ሊቀመንበር
No comments:
Post a Comment